ዜና
የመባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ የተቋሙ ዳሬይክተሮች፣ ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች እና የተቋሙ ሠራተኞች በተገኙበት ዛሬ መጋቢት 13/ 2017 ዓ.ም ሦስተኛ ቅርንጫፉን በመክፈት በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡
በቅርንጫፍ መክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የተቋሙ የዳሬይክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌትነት ኃይሌ ለተገኙት ታዳሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን መባዕ ሲቋቋም ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በመሆን በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማበርከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰብሳቢው አክለውም መባዕ ማይክሮ ፋይናንስን ልዩ የሚያደርገው ማበደር ብቻ ሳይሆን ተበዳሪዎች ውጤታማ የሚሆኑበትን የማማከር አገለግሎት የሚሰጥ መሆኑ ነው በማለት የገለጹ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙትም ይሁን ሌሎች የቁጠባ እና የብድር አገልግሎት በማግኘት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተጨማሪም አክሲዮን በመግዛት የመባዕ ዓላማ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ ማሞ በበኩላቸው የቅርንጫፉን ሥራ መጀመር አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርብ ጊዜ ወደ ኢንዱስትሪው የተቀላቀለ ቢሆንም ሥራ በጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራ መሥራቱን አንስተው በቀጣይም ተቋሙ ይዞት የተነሳውን ዓላማ ማሳካት እንዲችል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ ሦስተኛ የሆነውን ቅርንጭፍ በአዲስ አበባ ከተማ ጀሞ አካባቢ ጀሞ ሚካኤል ቅርንጫፍ በሚል ስያሜ የከፈተ ሲሆን በቀጣይ ግዜያት በአዲስ አበባ እና በክፍለ ሀገር ተጨማሪ ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት ተጠቁሟል፡፡
በቅርቡ ወደ ፋይናንስ ሴክተሩ የተቀላቀለው መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. አንደኛ መደበኛ እና አንደኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በራስ ዓምባ ሆቴል አካሒዷል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው፣ በተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት፣ የተቋሙን ካፒታል ማሳደግ፣ በውጪ ኦዲተር ሪፖርት እና መሰል አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የፋይናንስ ተቋሙን የገበያ ድርሻ ከፍ ለማድረግ የተቋሙን ካፒታል ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የተወያየው ጠቅላላ ጉባኤው፣ በቀጣይ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተቋሙን ካፒታል ወደ 300 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔን አሳፏል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባኤው 154 ዐዲስ ባለአክሲዮኖችን በመቀበል የባለአክሲዮኖችን ጠቅላላ ቁጥር ከአንድ ሺሕ በላይ አሳድጓል፡፡
መባዕ ማይክሮፋይናንስ አ.ማ. በሥነ ምግባር የታነጹ ብቁ የኾኑ ባለሞያዎችን በመያዝ፣ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ እየታገዘ ዜጎች የሚፈልጉትን የተቀላጠፈና ፍትሐዊ የፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ተገቢውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ጠንካራ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገልጿል።
የፋይናንስ ተቋሙ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት፣ የዝግጅት ሒደቱን አጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ በጠቅላላ ጉባኤው የቀረበው የዳሬይክተሮች ቦርድ ሪፖርት ያሳያል፡፡
በዚኽ ረገድ ተቋሙ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለከቱት የዳሬይክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌትነት ኀይሌ፣ ይህም መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ አክስዮን ማኅበርን፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አማራጭ ብቻ ሳይኾን ተመራጭም ያደርገዋል፤ ብለዋል።
የማይክሮ ኢኮኖሚ እና የፋይናንሻል ፖሊሲ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን መልካም ዕድሎችንና ስጋቶችን በማጥናት ተግዳሮቶቹን ለመቀነስና መልካም ዕድሎችን ለመጠቀም፣ የዳሬይክተሮች ቦርድ እና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩበት እንደሚኾን፣ የዳሬይክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው አስታውቀዋል።
ሰብሳቢው አቶ ጌትነት አያይዘውም፣ ተቋሙ በቂ የገበያ ድርሻ ማግኘትና በገበያው ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲኾን ካፒታሉን ማሳደግ፣ በከፍተኛ ኹኔታ ቁጠባ በመሰብሰብ የብድር ሥርጭትን ማሳደግ ወሳኝ የትኩረት አቅጣጫዎች ተደርገው መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡
ዜና
መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ የመጀመሪያ የሆነውን ቅድስተ ማርያም ቅርንጫፍ የተቋሙ የዳሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች እና የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በተገኙበት ዛሬ ሐምሌ 29/ 2016 ዓ.ም በመክፈት በይፋ ሥራ ጀመረ፡፡
በቅርንጫፍ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌትነት ኃይሌ ተቋሙ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልዕክታቸውም መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ ሥራ መጀመሩን የገለጹ ሲሆን ለባለአክሲዮኖችና ለተቋሙ አጋር አካላት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ አክለውም በሀገራችን በኢትዮጵያ በድህነት ውስጥ ያሉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎችን የፋይናንስ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ ዓላማውን ማሳካት እንዲችል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች፣ ለባለ አክሲዮኖች እና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጥሪ አቅርበዋል።
መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ የመጀመሪያ የሆነውን ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ 4 ኪሎ አካባቢ ቅድስት ማርያም ቅርንጫፍ በሚል ስያሜ በመክፈት ሥራ የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያት በአዲስ አበባ እና በክፍለ ሀገር ተጨማሪ ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ በይፋ ሥራ በመጀመር የፋይናንስ ዘርፉን ተቀላቀለ። ። ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ ፈቃድ በማግኘት በዛሬው ዕለት ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስሯል፡፡ የመባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌትነት ኃይሌ በተቋሙ የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ወቅት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ አብዛኛው ማኅበረሰብ በበቂ ሁኔታ በፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽ ሳይሆኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ አክለውም መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ በተደራሽነትና በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል ያለውን ክፍተት በማሻሻል ሰፊ መሠረት ያለው የአነስተኛ ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል የተቋቋመ መሆኑን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው የተቋሙ ምስረታ በስኬት እንዲጠናቅቅ ያገዙትን የአደራጅ ኮሚቴ አባላትን፣ ባለ አክሲዮኖችን እንዲሁም ሌሎች ደጋፊ አካላትንም አመስግነዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአሐዱ ባንክ የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ሰብስቤ በበኩላቸው አሁን በሀገራችን የሚታየውን የፋይናንስ አግለግሎት ክፍተት መፍታት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ይሄንን ችግር ለመፍታት የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ያላቸውን ተስፋ ገልጸው በቀጣይ አሐዱ ባንክ ከመባዕ ጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም መባዕ የጋራ ተቋማችን እንደመሆኑ ተቋሙን በጋራ ማሳደግ እንደሚጠበቅ ያስረዱት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ ማሞ ሲሆኑ ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ ሁለተኛውን ቅርንጫፍ የተቋሙ ሥራ አመራር አባላት፣ ጥሪ የተደረገላችው እንግዶች እና የተቋሙ ሠራተኞች በተገኙበት ዛሬ ነሐሴ 25/ 2016 ዓ.ም በመክፈት በይፋ ሥራ ጀመረ።
በቅርንጫፍ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ ማሞ ተቋሙ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ ሁለተኛው የሆነውን ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ሳሊተ ምሕረት ቅርንጫፍ በሚል ስያሜ ሥራ የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ግዜያት በአዲስ አበባ እና በክፍለ ሀገር ተጨማሪ ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱ ተጠቁሟል።